የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በመሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው በዋናነት ዜጎች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ጸጋ ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲያውቁ እና ሰብዓዊ ክብር ማክበርና መጠበቅ ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና መሰረት ዜጎች እምቅ ኃይላቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸው ንቁ፣ ደስተኛና ውጤታማ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ስልጠና መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የክትትል እና ምርመራ ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንደሰን ደሴ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በዋናነት በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በማድረግ እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የተለያዩ ምርምሮችን የሚያደርግ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
በስልጠናውም ስለ ሰብአዊ መብቶች ምንነት፣ መለያ ባህርያት፣የሰብአዊ መብቶች ታሪካዊ እድገት እና ለሰው ልጆች ያላቸው ፋይዳ ፣ ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፍ እንዲሁም መንግስት ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ ያሉበት ግዴታዎች እና ሰብአዊ መብቶች ከሌሎች መብቶች በምን እንደሚለዩ በሚሉት ርዕሶች ዙርያ ሰፋ ያለ ማብራርያ ተጥተዋል፡፡
በመድረኩም ከተሳታፊዎች በቀረበው ስልጠና ዙርያ የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓባቸዋል።


