መጪዉ ታህሳስ 19 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበረዉ ዓመታዊ የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታዉቋል::

የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ለሚዲያ አካላት በበአሉ አከባበርና እንግዳ አቀባበል ዙሪያ መግለጫ ሰተዋል።

ክቡር ኮሚሽነር አለሙ መግራ በመግለጫቸው በዓሉ ያለምንም የፀጥታ እና የትራፊክ አደጋ ችግር እንዲከበር ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ረጅም ጊዜ የፈጀ ዝግጅት መደረጉን ገለፀው እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ የንግስ በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በአሉን ለመታደም ከመላው የሀገራችን ክፍሎች እና ከተለያዩ አለም ሀገራት የሚመጡ እንግዶች በከተማችን በሚያሳልፏቸው ቀናቶች ሰላማቸው ተጠብቆ ምንም አይነት የወንጀል እና የትራፊክ አደጋ እንዳይገጥማቸው ከዛም ባለፈ በሁሉም ቀጠና ለእንግዶች ማረፊያ ይሆን ዘንድ ድንኳኖችን በማዘጋጀት እንግዶችን በፍቅር ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደስራ የተገባ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሉ የሚከበረው በሜታ ወረዳ ቁልቢ ከተማ ይሁን እንጂ ከበአሉ አስቀድሞ እንግዶች በከተማችን ድሬዳዋ በሚያደርጉት ቆይታ አንድም ስጋት ሳይገባቸው ቀንም ለሊቱም ድሬዳዋ ሰላም በመሆኗ የለሊት የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም ገልፀዋል።

ይህ በአል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የምስራቅ ኢትዮጵያ የጋራ ደህንነት ግብረ ሀይል በቅንጅት የፀጥታውን ስራ እየሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር አለሙ መግራ ጨምሮ ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *