ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር በዳሰነች ወረዳ በድሮን የታገዘ የክትባት ስርጭት በይፋ ጀመረ::

የጤና ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ጋር በመተባበር፣ የማርበርግ ቫይረስ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የህይወት አድን መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በድሮን የማድረስ ስራ ዛሬ በይፋ ጀምሯል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታትና ራቅ ያሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ በወሰደው የፈጣን ምላሽ እርምጃ፣ ዛሬ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዳሰነች ወረዳ በድሮን የታገዘ የክትባት ስርጭት በስኬት ተከናውኗል።

የዳሰነች ወረዳ ካለው ራቅ ያለ መልክዓ ምድር አኳያ በመኪና ለማጓጓዝ ረጅም ሰዓታት ይወስድ የነበረውን ጉዞ፣ በድሮን በመታገዝ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ክትባቱን በ –80°C ቅዝቃዜ ጠበቆ በማድረስ ለአካባቢው ማህበረሰብ ክትባቱን መስጠት ጀምሯል።

ይህም ተግባር የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት (EPSS) የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገሩን በተግባር ያሳየበት ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ወረርሽኞችን ለመመከት የራሷን የውስጥ አቅም እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም መጀመሯን የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ ሲሆን፣ በቀጣይም ይህ በድሮን መድኃኒት የማድረስ አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

Ministry of Health,Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *