በወረዳ ሁለት (02) እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ለወረዳው በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃት እየፈጠረ እንደሚገኝ የወረዳው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በድሬዳዋ በወረዳ ሁለት አስተዳደር

በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአኪር ድልድይ(ከሰብሪያ ሪዞርት) እስከ ቻይና ድልድይ እንዲሁም ከብሪጅ ድልድይ እስከ ማደያ እና ከመስቀለኛ እስከ ሸረፍ ሆቴል ሰባተኛን አጠቃሎ ባሉት አካባቢዎች እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም የኮሪደር ልማቱ እየተከናወነባቸው የሚገኙ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ልማቱ ለወረዳው በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃትን እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በወረዳው የሚገኙ የእግረኛ መንገዶች የተጣበቡና የተዘጋጉ እንደነበረ ነዋሪዎቹ ጠቅሰው በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገዶችን የመክፈትና የማስፋት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ነዋሪዎቹ አያይዘውም ለአካባቢው ውበት የሌላቸው ወጥ ያልሆኑና ያረጁ ቤቶችን

ወጥ የማድረግና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአዲስ የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው ይህም ለወረዳው ማራኪ ገፅታን እያላበሰው እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን በቀጣይም ልማቱን አጠናክረን እናስቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው ደጋፊ አመራር የሆኑት አቶ ገበየሁ ጥላሁን “እኔ ለመንደሬ ምን ሰራው” በሚል ውብ ወረዳን ለመፍጠር ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመሆን አካባቢን የማስዋብ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ወረዳው ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስራዎችን በቡድን በመከፋፈል እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ገበየሁ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የወረዳ ሁለት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ በበኩላቸው በኮሪደር ልማቱ መንገድ ዳር የሚገኙ የንግድና የመኖሪያ ቤትችን ቁመታቸውን የማሳደግና ወጥ የማድረግ እንዲሁም ቀለም የመቀባት ስራዎች፣ የሻዶ ላይትና ስትሪፕ ላይት ስራዎች በተጨማሪም 20 ሜትር ራዲየስ የመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም 50 ሜትር ራዲየስ የግልና የመንግስት ተቋማት ዙሪያቸውን እንዲያፀዱ የማድረግ ስራ በተጨማሪም የንግድ ሱቅ በሮችን በአልሙኒየም የመተካት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

አቶ አቤል አያይዘውም በልማቱ ከ 6 መቶ 81 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

በኮሪደር ልማቱ በሁለተኛው ምዕራፍ ከመስቀለኛ እስከ ገንደ ተስፋ እንዲሁም ከጀርባ አስፓልት እስከ ሀሎሌ ፓሊስ ጣቢያ ጫፍ ድረስ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ የአካባቢ ልማትና የህብረተሰብ ተሳትፎ ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅና የወረዳው ደጋፊ አመራር የሆኑት ወ/ሮ ረሂማ አወል ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *