በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት 6 ወራት በህገ-ወጥ መልኩ ሊወጡና ሊገቡ የነበሩ ከ 1.7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ምርቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ::

በድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት (የ6 ወራት) የፀረ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ መከላከል፣ የኑሮ ውድነት መቀነስና ዋጋ ማረጋጋት እንዲሁም ኤክስፖርት ምርት ማሳደግ የጋራ ግብረ-ኃይል ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በዛሬው ዕለት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ባለፉት 6 ወራት በተቀናጀ አግባብ ኤክስፖርት ላይ በመሰራቱ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በመደጉም ባለፉት 6 ወራት ከቡና፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከቅመማ ቅመም፣ ከግብርና ምርቶች እንዲሁም ወደ ውጪ ከሚላኩ የቁም እንሰሳት 111.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የገለፁት ም/ከንቲባው ይህም የሀገራችንን የማክሮ ኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የጎላ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) ኮትሮባንድን የመቀነስና ኤክስፖርትን በላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በአጠቃላይ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ስራዎችን በቅንጅት በመስራት የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገርና በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ጫና የመቀነስ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የተሰሩ ጠንካራ ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባና የታዩ ክፍተቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም በኮትሮባንድ ቁጥጥር ላይ የተቀናጀ ስራ መሠራት አስፈላጊ መሆኑን ም/ከንቲባ ሀርቢ ጠቁመዋል።

በአስተዳደሩ ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጠሃ የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት (የ6 ወራት) የፀረ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ መከላከል፣ የኑሮ ውድነት መቀነስና ዋጋ ማረጋጋት እንዲሁም ኤክስፖርት ምርት ማሳደግ የጋራ ግብረ-ኃይል ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *