የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
1ኛ. ካቢኔው በቀዳሚነት የተወያየው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ በአጋርነት የተለያዩ የልማት ስራዎችን በጋራ ማከናወን እንዲችሉ የወጣው ደንብ ላይ ነው።
በዚህም የግሉ ዘርፍ ለሀገራዊ እድገትና ልማት መሰረት በመሆኑ በአስተዳደሩ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ሚና መወጣት እንደሚገባው ካቢኔው የጠቆመ ሲሆን በአጠቃላይ ከቤቱ የተነሱ ሃሳብ አስተያየቶች በደንቡ ላይ ተካተው በቀጣይ ወደ ስራ እንዲገባ ካቢኔው ወስኗል።
2ኛ. ካቢኔው በመቀጠል ከመሬትና መሬት ነክ ጋር የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥናቶች ላይ በጥልቀት ተወያይቷል።
በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችም በቀጣይ በጥናቱ ተካተው ጥናቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፀድቆ ወደ ስራ እንዲገባ ካቢኔው ውሳኔ አስተላልፏል።
3ኛ. በመጨረሻም ካቢኔው በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ በመሰማራት የአስተዳደሩን የልማት ጉዞ ለማፋጠን ታሳቢ በማድረግ
ለአስተዳደሩ የቀረቡ የመሬት አቅርቦት ጥያቄዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም ካቢኔው የቀረቡት የመሬት አቅርቦት ጥያቄዎች ተገቢነትና የመሬት አቅርቦት ጥያቄ ያቀረቡ አልሚዎች በቀጣይ ተሰማርተው የሚሰሩባቸው ዘርፎች ለአስተዳደሩ የሚሰጡት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ለይ በዝርዝር በመወያየት ውሳኔ አስተላልፏል።


