እንደ ገዥ ፓርቲ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን እና ያለፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም የግምገማ መድረክ የሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሁሉም የምርጫ ክልሎች የሰላም ሁኔታ ያለበት ደረጃ ተለይቶ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችሉ የሰላም እና ፀጥታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ገልጸዋል።
እንደ ፓርቲ በምርጫው በብቃት ለመሳተፍ ዝግጅቶች መደረጉን ጠቁመው፣ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የፓርቲ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት እና ተሞክሮዎችም የተወሰዱበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የልማት ሥራዎችን የሕዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መንገድ በመምራት ዘላቂ ሰላምንም ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለም ገልጸዋል።
የፓርቲው ኢኒሼቲቮች እና ሰው ተኮር ሥራዎች አፈጻጸም የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነ ገልጸው በዚህም የሕዝብ ተሳትፎ የላቀ እንደሆነ አብራርተዋል።
በየአካባቢው ያሉ እምቅ አቅሞችን ለይቶ በመጠቀም ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር ኅብረብሔራዊ ወንድማማችነት /እህትማማችነት/ ትርክት እንዲጎለብት ተደርጓል ያሉት አቶ አደም ፋራህ፣ በዚህም ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የፓርቲ ዕሳቤዎችን በአግባቡ የተረዳ አመራር ለመፍጠር በተሠሩ ተግባራት የአመራር ብቃት አድጓል፤ በዚህም ፓርቲያችንን በአደረጃጀት እና በአሰራር ማጠናከር ተችሏል ብለዋል።
የጋራ ትርክት የበላይነትን ለማስረፅ በሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን የተሠሩ ተግባራት በርካታ ስኬቶችን ስለማስመዝገባቸውም አንሥተዋል።
አቶ አደም ፋራህ እንዳብራሩት ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች የፓርቲውን የሕዝብ ቅቡልነት ማሳደግ ተችሏል።
ፓርቲው የልማት ሥራዎችን በብቃት መምራት በመቻሉ የሕዝቡ አመኔታ ጨምሯል። ለዚህም ማሳያው በልማት ሥራዎች በቀዳሚነት መሳተፉ እና ጥያቄዎቹንም በሕዝባዊ መድረኮች በግልጽ ማቅረቡ ነው ሲሉ ማብራራታቸውን ከፓርቲው ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


