የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ሥራዎች አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በጥንታዊነትና በጀግንነት ታሪክ በሚታወቀው የሀዲያ ሕዝብ መሀከል በሆሳዕና ከተማ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ሲሉ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋናው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
በአጠቃላይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የፓርቲው የልማት ውጥኖች በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረጉ ፍሬ እያፈሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የፓርቲው ጉዞ የሕዝብን የላቀ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ውጤቶች የታጀበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አደም፣ የሆሳዕና ከተማም በጠንካራ የሥራ ባህልና በማኅበራዊ ትስስር የምትታወቅ መሆኗን አመልክተዋል።
ከግምገማ መድረኩ ጎን ለጎን የሰላም አምባሳደር በሆነችውና በፍጥነት በማደግ ላይ ባለችው በሆሳዕና ከተማ እየተሰሩ የሚገኙ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን አቶ አደም አስታውቀዋል።
የጉብኝታቸው ቅድመ መዳረሻ እጅግ ባጠረ ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው የርዕሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት መሆኑን የገለጹት አቶ አደም፣ ተቋሙ በክልሉ ለሥራ ምቹ የሆኑ የሥራ አካባቢዎችን ለመፍጠር ለተያዘው ግብ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ተግባር ሆኖ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ እምብርት ላይ የተገነባው የአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሌላኛው የጉብኝቱ አካል እንደነበር የጠቆሙት ኃላፊው፣ ስታዲየሙ ወጣቶችን በስነ-ምግባር አንፆ ለማሳደግና የስፖርቱን ዘርፍ ለመደገፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ይህ ስፖርታዊ መሰረተ ልማት ብልፅግና ፓርቲ በማህበራዊ ዘርፍ ለሚያከናውናቸው ተግባራት አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑንም አቶ አደም ፋራህ አብራርተዋል።
የታላቁን የሀዲያ ህዝብ ወግ፣ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ አጣምሮ የያዘውና “ሀዲይ ነፈራ” (የሀዲያ ደጃፍ) ተብሎ የተሰየመው የባህል መንደር መጎብኘቱንም ጠቁመዋል።
ይህ የባህል መንደር በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፍ እየታዩ ላሉ መነቃቃቶች ሁነኛ ማሳያ ሊሆን የሚችል እንቅስቃሴ መሆኑን አቶ አደም በአጽንኦት ገልጸዋል።
በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው የ12.5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት የጉብኝቱ ማጠቃለያ እንደነበር የገለጹት አቶ አደም፣ ስራው ዘመናዊነትን ከባህላዊ ትሩፋቶች ጋር ያጣመረ መሆኑን አስታውቀዋል።
ልማቱ ዘመናዊ የእግረኛ መንገድ፣ የአውቶቡስ መጠበቂያና ስማርት የኤሌክትሪክ ፖሎች የተገጠሙለት ከመሆኑ ባለፈ አካል ጉዳተኞችን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።


