“የወረዳ 07 የኮሪደር ልማት ለአካባቢው ንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው” – በወረዳ 07 የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ።

በድሬዳዋ ወረዳ 07 እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ለአካባቢው ንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን በወረዳው የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብና ነዋሪዎች ገለፁ።

ከኮሪደር ልማቱ በፊት አካባቢው ባረጁ ቤቶች፣ በሸራና በማዳበሪያ የተሞላ እንደነበረ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ በአሁኑ ሰዓት በኮሪደር ልማቱ የንግድ ሱቆችን በአዲስና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመገንባት ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝና ይህም ለአካባቢው ውበት እየሰጠው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም አካባቢው የንግድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከድሬዳዋ ውጪ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለግብይት እንግዶች የሚመጡበት ስፍራ በመሆኑ ባማረና የድሬዳዋን የልማት ግስጋሴ በሚመጥን መልኩ መሰራቱ የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት እንደሚጨምረው ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው ደጋፊ አመራር ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በወረዳው ከ 2 ሺ በላይ የንግድ ሱቆችና ከ10 በላይ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ሰዓት የኮሪደር ልማቱ በአጠቃላይ ከ 6 ኪ.ሜ በላይ ዋና ዋና መንገዶችን አካቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንጂነር ጀማል አያይዘውም ከአልፈሪድ ሻፊ(ኮኔል ድልድይ) እስከ ክርስቶስት ት/ቤት እንዲሁም ከኮኔል ጫፍ እስከ አሸዋ (አላይበዴ ጫፍ)፣ ከቀላፎ እስከ መጋላ ጨብዱ አብዱላሂ መዘጋጃ ድረስ እንዲሁም የታይዋንና የአላይበዴ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጨምሮ በኮሪደር ልማቱ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዋናነት በኮሪደር ልማቱ በመንገድ ዳር የሚገኙ ንግድ ቤቶችን በአልሙኒየም ክላዲንግ፣ በስቶን በክላዲንግ፣ በቀለምና በመብራት የማሳመር ተግባር በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ኢንጂነር ጀማል ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡ ከልማቱ ጎን በመቆም የንግድ ሱቆችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመገንባትና አካባቢውን የማሳመር ስራ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩ ኢንጂነር ጀማል፤ በቀጣይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የወረዳ 07 አስተዳደር ጽ/ቤት ዋና አፈጉባዬ አቶ በረከት አባስ በበኩላቸው አካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት መሆኑን ጠቅሰው ኮሪደር ልማቱ በፊት በከፍተኛ ሁኔታ የእግረኛ መንገዶች በተለያዩ ቁሳቁሶችና ህገ-ወጥ የቆርቆሮ ቤቶች ተዘግተው እንደነበረ ገልፀዋል።

አቶ በረከት አያይዘውም በኮሪደር ልማቱ መንገዶችን የማስከፈትና የማስፋት ስራ እንዲሁም ሱቆችን ለንግድ ምቹና ለአይንም ሳቢ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *