“መልካጀብዱ ከአቧራና ከቁሻሻ ተላቆ ውበትን እየተጎናፀፈ ይገኛል” – የወረዳ 01 ነዋሪዎች::

በድሬዳዋ በወረዳ 01 እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ አካባቢውን ከአቧራና ከቁሻሻ አላቆ አዲስ ውበትንና ገፅታን እያጎናፀፈው እንደሚገኝ የወረዳው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በዚህም የወረዳው ነዋሪ የሆኑት አቶ ነብዩ ደመቀ ከዚህ ቀደም የመልካ ጀብዱ መንገድ የተዘጋጋ በቁሻሻና በአቧራ የተሞላ እንደነበረ አስታውሰው፤ በአሁን ሰዓት በኮሪደር ልማቱ መንገዶች ተከፍተው ባማረ መልኩ እየተሰሩ እንደሚገኙና ይህም ለወረዳው አዲስና ማራኪ ገፅታን እያላበሰው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ወረዳው ሳቢ ያልሆነ ገፅታ እንደነበረው የገለፁት ደግሞ ወ/ሮ ሁሪዮ አብዱላሂ ሲሆኑ በአሁኑ ሰዓት በኮሪደር ልማቱ ወጥ በሆነ መልኩ ለአካባቢው ውበት የሚጨምሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

ወ/ሮ ሁሪያ አያይዘውም በቀጣይም የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ስራ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ገልፀው አካባቢያቸውን በማፅዳትና ችግኞችን በመትከል የማስዋብ ስራን እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳ አንድ ደጋፊ አመራር የሆኑት አቶ ፉአድ መሀሙድ በወረዳው ወደ ኢንደስትሪ ፓርክ የሚያደርስ ሀይዌይ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በመንገዱ ዳርም የድሬዳዋን ውበት የሚያጎሉ ዘመናዊ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ፉአድ አያይዘውም በወረዳው በሚገኙ 6ቱም ቀጠናዎች በተቀመጠው እስታንዳርድ መሰረት ቀለም የመቀባት ስራዎች ፣ በመብራት የማስዋብና 20 ሜትር ራዲየስ የመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም 50 ሜትር ራዲየስ የግልና የመንግስት ተቋማት ዙሪያቸውን እንዲያፀዱና የአረንጓዴ ልማት ስራን እንዲተገብሩ የማድረግ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኘውን የወረዳውን የኮሪደር ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ስራዎች በየቀኑና በየሁለት ቀኑ ከአስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን እንደሚገመገሙም አቶ ፉአድ ገልፀዋል።

በሞዴል ቀጠናዎች የቀለም ስራ ማለቁን የጠቆሙት ደግሞ የወረዳ 01 ስራ አስኪያጅ አቶ ሁሴን አህመድ ሲሆኑ የልማት ስራው በወረዳው ብሎም በአስተዳደሩ ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *