የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ በዛሬው ዕለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል::

ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም

ድሬዳዋ

የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

1ኛ. ካቢኔው በቀዳሚነት የድሬዳዋ ስማርት ሲቲ ኢኒሼቲቭን ማፋጠን በሚቻልበት አጀንዳ ላይ በመወያየት ውሳኔ አስተላልፏል።

የስማርት ሲቲ ስራዎች ከሰው ንክኪ ነፃ የሆኑና የህዝብን ደህንነትን በመጠበቅ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመስጠት የሚያስችል ነው። የድሬዳዋ አስተዳደርም “የስማርት ድሬን” ጉዞ ለማፋጠን አሰራሮችን በዲጂታል የመቀየር ተግባራትን በስፋት እያከናወነ ሲገኝ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

2ኛ. ካቢኔው በመቀጠል ኤች አይ ቪ /HIV AIDS/ በደማቸው ለሚገኙ ወገኖች ማህበራት የሰብዓዊ አገልግሎት የበጀት ድጋፍ ማሻሻያ ጥያቄ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ማገዝ የሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

3ኛ. ካቢኔው በአስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፤ በሮድ ፈንድ የ 5 ኪ.ሜ የአሰፓልት ጥገና እና ኦቨር ሌይ ስራ ሬንጅ በመንገዶች ባለስልጣን በማቅረብ የማሽነሪና የሰው ሀይልን በመጠቀም ስራዎቹ እንዲከናወኑ ካቢኔው ውሳኔ አስተላልፏል።

4ኛ. በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የተከናወነባቸው እና ሌሎች ተከናውነው የተጠናቀቁ የአስፓልት መንገዶቸ ላይ የተለያዩ ጠቋሚ የመንገድ ላይ ምልክቶችንና የእግረኛ መሻገሪያ ዜብራ ምልክቶች በፍጥነት እንዲከናወን ውሳኔ ተላልፏል።

በመጨረሻም ካቢኔው በልማትና በሌሎችም መሰል አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *