ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ሚና የሚያሳድጉ ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግባለች – ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

ዛሬ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ዱባይ በተጀመረው የ2026 የዓለም መንግሥታት ጉባኤ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ሚና የሚያሳድጉ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ወቅት ኢትዮጵያ ከእገዛና ጥገኝነት ወጥታ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሯንና አፍሪካም የዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተመልካች ብቻ ሳትሆን ዋነኛ ተዋናይ መሆን የምትችልበት ጊዜ ላይ መሆኗን አስገንዝበዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶችን ለዓለም መሪዎች ያስረዱት ፕሬዚዳንት ታየ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሜጋ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዘርፍ ግንባር ቀደም እንደሚያደርጋት አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት መሸጋገሯን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 640 ሺህ ቶን ቡና በማምረት አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧን አስታውቀዋል።

የዓለም አቀፍ የግንኙነት ሥርዓት ፍትሐዊ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው፤ ኢትዮጵያ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን ባከበረ መልኩ ከማንኛውም ወገን ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

አፍሪካ የ1.3 ቢሊዮን ሕዝብና የ3.4 ትሪሊዮን ዶላር የጋራ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያላት አህጉር መሆኗን በመጥቀስ፤ የአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ለአፍሪካ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *