የስፖርት ሜዳዎችን ከኮሪደር ልማቱ ጋር በማስተሳሰር ምቹና ሳቢ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ::

የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከሳቢት ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር የሳቢያን ሜዳ አፈር ማልበስ እና ለስፖርታዊ ግጥሚያዎች ምቹና ሳቢ የማድረግ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌደሬሽን የውድድርና ስነ-ስርአት ዋና ሰብሳቢ ወጣት ኤርሚያስ ሀይሉ ገልፀዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጀሀር ሀሳብ አመንጪነት የሜዳ ሙሌት ስራ እንዲሁም ሜዳውን ለመጫወቻ ምቹና ሳቢ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ወጣት ኤርሚያስ ተናግረው፤ የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኃላ በኮሚሽነር አለሙ መግራ እየተመራ “ኳሱ የኛ ነዉ” በሚለዉ መርህ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማት ስራዎች ለድሬዳዋ ከፍተኛ መነቃቃትን የፈጠሩ መሆናቸውን ወጣት ኤርሚያስ ተናግረው የስፖርት ሜዳዎችን ከኮሪደር ልማቱ ጋር በማስተሳሰር ምቹና ሳቢ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በበኩላቸው ሜዳው አንጋፋና በርካታ ተጫዋቾችን ያፈራ መሆኑን ገልፀው አሁን ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የማሻሻያ ስራ ለተጫዋቾች ምቾትን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *