39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔና የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በስኬት መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤና 2ኛው የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በስኬት መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ፤ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደኅንነት የበለጠ በማጠናከር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እጀባና አስተማማኝ ጥበቃ በማድረግ ጉባኤዎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ ማስቻሉን ገልጿል።

መላው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አመራርና አባላት የተሰጣቸውን ግዳጅ በጥብቅ ዲሲፕሊን ለአፍታም ሳይዘናጉ 24/7 ሰርተው በመወጣታቸው እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተባብረው በመሥራት እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅ በሚያጋጥምበት ወቅት በትዕግስት ጠብቆ እንግዶችን በማሳለፍ ላደረጉት ቀና ትብብር ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የማስከበር ሥራው እንግዶች ወደ የሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ያስታወቀው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *