ኢትዮጵያን በሐሳብና በዕውቀት የመምራት ውጤቱ በልማት ሥራዎች እየተንፀባረቀ ነው – አቶ ተመስገን ጥሩነህ

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገርን በሐሳብና በእውቀት የመምራት ውጤቶች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልጹ።

የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ በተመረቀበት ወቅት አቶ ተመስገን በአደረጉት ንግግር፤ ቀደም ሲል በሀገሪቱ የነበረው ትልቁ ፈተና የሐሳብና የራዕይ ማነስ እንደነበር አስታውሰዋል።

እነዚህን ክፍተቶች በመሙላትና ለተግባራዊነቱም ሌት ከቀን በመሥራት፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በግልጽ የሚታይ የዕድገትና የለውጥ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

አቶ ተመስገን አክለውም፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ የታደሙ ልዩ ልዩ የአፍሪካ መሪዎች በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ አድንቀው ማለፋቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ ስኬት በመደመርና በአንድነት የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለሰላምና ለልማት መጠናከር መላው ማኅበረሰብ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ገና ያልተነካና ያልለማ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት እነዚህን ሀብቶች ለማልማት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን አብራርተዋል።

ዛሬ የተመረቀው የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ፣ ለውጭ ሀገር ምርት ግዢ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀር ተናግረዋል። ፋብሪካው ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ፣ የኢንዱስትሪ ሽግግርን እንደሚያፋጥንም አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *