ከትላንት ቁጭት እስከ ዛሬው የልማት ፀሐይ፤ የወለጋ አዲስ ገጽታ

ተፈጥሮ ሳትሰስት ጸጋዋን የቸረችው፣ ለም መሬትና ማዕድናት የሞሉበት፣ ምቹ አየር የታደለው የወለጋ ምድር፤ ለዘመናት የጸጋውና የገጽታው መራራቅ የሕዝቡ የቁጭት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

የአካባቢው ሕዝብ አጠገቡ እያየውና እየዳሰሰው በቁጭት የሚንገበገብለት የተፈጥሮ ሀብት ለምቶ ኑሮው እንዲሻሻል የዘመናት ምኞቱ ነበር። ይህን የሕዝብ መሻት የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰባት ዓመታት በፊት በነቀምት ከተማ ተገኝተው ከሕዝቡ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ሕዝቡ የዘወትር ጥያቄው ልማትና ዕድገት መሆኑን በአንድ ድምጽ አሰምቶ ነበር።

በወቅቱ ሕዝቡ “መሻትና ሀብት ሳያንሰን፣ ለለውጥ የሚተጋ መሪ አጥተን ምኞታችን ቀረ” ሲል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ላይ ያለውን ጽኑ እምነት ገልጾ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በወቅቱ ምላሽ ሲሰጡ “ልማት ያለ ሰላም አይታሰብም፤ ሰላማችሁን ጠብቁ፤ ልማቱ በጊዜ ሂደት ይታያል” የሚል የቁርጠኝነት ቃል ገብተው ነበር።

ዛሬ ያ የትላንት ቃል በተግባር ተተርጉሞ በወለጋ ምድር የልማት ፀሐይ ወጥታለች። “የመደመር መንግሥት” የማይተገብረውን ቃል እንደማይገባና ቃል የገባውን ደግሞ በተግባር እንደሚያሳይ በዚህ የልማት ውጤት ታይቷል። ትላንት መንግሥት በወለጋ አካባቢ ልማት እንደሚያመጣ የተናገረው ቃል ዛሬ በነቀምት ከተማና በአካባቢዋ በታዩት ለውጦች እውን ሆኗል።

አሁን በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታየው ዕድገት ወለጋንም አድምቋል። ይህም መንግሥትና ሕዝብ በቅንጅትና በሰላም እጅ ለእጅ ተያይዘው ከሠሩ የማይቻል ነገር እንደሌለ ትልቅ ማሳያ ሆኗል። ትላንት በቁጭት የሚታየው የተፈጥሮ ሀብት፣ ዛሬ በልማት እየተቀየረ የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል ጀምሯል።

ኢትዮጵያ ስትሠራ ትታያለች፤ ስትለማ ትከበራለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *