የተጀመረውን ልማት እና ብልፅግና ለማስቀጠል ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የተጀመረውን ልማት እና ብልፅግና ለማስቀጠል ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቄለም ወለጋ ዞን የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን በጎበኙበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኦሮሞ ሕዝብ ሰላም ወዳድ መሆኑን ለማሳየት ልጆቹን ነጋሳ እና ነጋሶ በማለት ይሰይማል ብለዋል።

ሕዝቡ ሰላም ዋነኛ እሴቱ እና መለያው እንደሆነ ገልጸው፤ ልዩነትን በውይይት እንደሚፈታ ለማሳየት ልጆቹን አራርሳ (አስታራቂ) ብሎ የሚሰይም ድንቅ ጥበብ የተጎናጸፈ ሕዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

በየትኛውም ግጭት ሊደፈርስ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፤ ችግሩን በንግግር እና በውይይት መፍታት ጥበብ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የወለጋ አካባቢ ባለፉት ጊዜያት የሰላም እጦት ገጥሞት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተጀመረውን ልማት እና ብልፅግና ለማስቀጠል ሰላምን ማጽናት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

ልዩነቶች ቢያጋጥሙ እንኳን በምክክር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በትጥቅ ትግል ጫካ የነበሩ ወንድሞች ፍላጎታቸውን በውይይት ለማሳካት ማህበረሰቡን መቀላቀላቸው በመቻላቸው አድናቆታቸውን ገልጸው፤ የቀሩ ወንድሞችም በሰላማዊ መንገድ ህብረተሰቡን ተቀላቅለው የተጀመረውን ልማት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አካባቢው ያለውን የቡና እና እንስሳት ልማት እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ሰላምን ማጽናት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

አሁን በአካባቢው የታየው የልማት ጭላንጭል ወደ ተሟላ ብርሃን እንዲሸጋገር ሁሉም ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

ልዩነቶችን እና የፖለቲካ ፍላጎቶችን በውይይትና በንግግር ብቻ መፍታት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ሕዝቡ ጫካ ያሉ ልጆቹን በመምከር እና በመገሰጽ የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ግፊት በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች እና ምሁራን ሰላምን በማጽናት ሂደት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ነው ያሉት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *