የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር ያፋጥናል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ

የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ በይፋ መመረቁ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያስፈነጥር መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋብሪካውን መመረቅ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፋብሪካው በተለይም ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ከዚህም ባለፈ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ለኃይል አቅርቦት የሚያወጡትን የማጓጓዣ ወጪ በመቀነስ ረገድ ፋብሪካው ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በበርካታ ዘርፎች ራሷን የመቻል ጉዞ ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፤ ይህም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በሁለንተናዊ መልኩ ምሉዕ እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ትገሠግሣለች” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መሰል የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገራዊ ብልፅግና ያላቸውን ፋይዳም አፅንኦት ሰጥተውበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *