የኢትዮጵያ የትንሳኤ ጉዞ፦ ከመጋቢት እስከ መጋቢት የከፍታና የብርሃን ስምንት ዓመታት

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ አውድ ውስጥ መጋቢት ወር የድልና የነፃነት ተምሳሌት ነው። ጥንት በየካቲት ወር መጨረሻ ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የታወጀበት ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም አዲስ የለውጥ ማዕበል ይዞ ብቅ ማለቱ ይታወሳል።

ከመጋቢት 2010 እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም ባሉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስብስብ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር፣ የማይታመኑ አሻራዎችን ያሳረፈችበትና ሁለንተናዊ ገጽታዋን የቀየረችበትን አዲስ ምዕራፍ እውን አድርጋለች።

ይህ የለውጥ ጉዞ በፖለቲካው መስክ መሠረታዊ የሆነ የትርክት ሽግግር ያመጣ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የነበረውን በዜጎች መካከል የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ስሜት የፈጠረ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎችን ብቻ የበላይና ባለቤት ያደረገውን በመቀየር ሁሉንም ህዝቦች እኩል ባለቤት ያደረገ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን አንግሷል።

“መደመር” በተሰኘው ሀገራዊ ፍልስፍና የታገዘው ይህ ጉዞ፣ ኢትዮጵያውያን ከታሪክ እስረኝነት ወጥተው ካለፈው ስህተት እየተማሩና መልካሙን እያወረሱ ወደፊት እንዲራመዱ የሚያስችል አሰባሳቢ ትርክት እንዲገነባ አድርጓል።

በዚህም በዜጎች መካከል ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን፣ ከጥርጣሬ ይልቅ መተማመንን የሚያጎለብት አዲስ የፖለቲካ ባህል መሠረት ይዟል።

የዲሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛና ነፃ የማድረጉ ተግባር የለውጡ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። ቀደም ሲል የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆነው የቆዩት እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የፍትሕ አካላት ተቋማዊ ነፃነታቸውን አግኝተው ሀገርንና ህዝብን በማገልገል መርህ እንዲደራጁ መደረጋቸው የዲሞክራሲ ሥርዓት ዘላቂነት ዋነኛው መሠረት ሆኗል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡት ድሎች የኢትዮጵያ የትንሳኤ ጉዞ የማይቀለበስ መሆኑን የሚያረጋግጡ፣ በጽናት የተሻገርች አይበገሬ ሀገር በመሆን ለተተኪው ትውልድ ተስፋን የሚሰነቁ ደማቅ የታሪክ አሻራዎች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *