ኢትዮጲያን ወደ ተምሳሌት ሀገር በሚል መሪ ሀሳብ የ 2018 ዓ.ም 7 ተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎችን የማስተዋወቅ መርሀ-ግብር በዛሬው እለት በቢዮአዋሌ ክላስተር ተካሂዷል።
በመርሀ-ግብሩ ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ብልፅግና ፓርቲ ያለፍትን የለውጥ አመታት እንደ ሀገር በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል ።
ከዚህ ቀደም የነበሩትን የኢኮኖሚ ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ስብራቶችን በመጠገን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ኢብራሂም ገልፀው ብልፅግና ፓርቲ 7 ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሲወዳደር ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ፣ ፍትሀዊ እንዲሁም ደግሞ ነፃ እና ተአማኒ ምርጫ እንዲሆን እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት።
ብልፅግና ፓርቲ በ 7 ተኛው ሀገራዊ ምርጫም በትምህርት ዝግጅታቸው ፣ በስነ-ምግባራቸው እና በስራ አፈፃፀማቸው የታመነባቸውን ለእጩነት እንዳቀረቡም ነው አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በእለቱ ያስታወቁት ።


