የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ከሪማ አሊ ለሚካሄደው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ የሚያበቃቸውን የመራጭነት ካርድ ወስደዋል።
ምክትል አፈጉባኤዋ በዛሬው ዕለት በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ በመገኘት ነው የመራጭነት ካርዳቸውን የወሰዱት።
ካርዳቸውን ከወሰዱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል። ማንኛውም መራጭ የመምረጥ መብቱን ለመጠቀም መጀመሪያ የመራጭነት ካርድ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም ሴቶችና ወጣቶች በምርጫው ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የራሳቸውንና የአገራቸውን መፃኢ ዕድል እንዲወስኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ምርጫ ካርድ የመውሰጃው ጊዜ ሳይጠናቀቅ ሁሉም የድሬዳዋ ነዋሪዎች ወደየምርጫ ጣቢያዎቻቸው በመሄድ ካርዳቸውን እንዲወስዱ አሳስበዋል።


