የድሬዳዋ የንግድ ምልክት እና የታሪክ መዘክር የሆነው ታሪካዊው የቀፊራ የገበያ ማዕከል፣ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ በዘመናዊ መልኩ ታድሶ ዛሬ በይፋ ተመረቀ።
ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ የንግድና የባህል ማዕከል ሆኖ የቆየው ይህ ስፍራ፣ የነበረበትን የጽዳትና የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በመቅረፍ ለከተማዋ አዲስ ድምቀት ሆኗል።
የማዕከሉ ጥንታዊ የህንጻ ጥበብ እና ታሪካዊ ቅስቶች (Arches) ሳይቀየሩ ጸንተው እንዲቆዩ ተደርጓል።
ነጋዴዎችን ከጸሐይና ከዝናብ የሚከላከሉ ዘመናዊ መጠለያዎች (Sheds) እና የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃዎች ተገንብተውለታል።
ማዕከሉ በዘመናዊ መብራቶች በመደምቁ ለምሽት ግብይትና ለደህንነት ምቹ ሆኗል።
ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እንደገለጹት፤ ቀፊራ ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀረርጌ፣ ለሶማሌ ክልልና እስከ ጅቡቲ ድረስ ምርት የሚያከፋፍል የንግድ ዋልታ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ “የእናት ጓዳ” የተባለለትን ይህን ስፍራ ከነበረበት የተዘበራረቀ አሰራር ማውጣት መቻሉን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከንግድ ባለፈ የከተማዋ ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ሆኖ እንዲያገለግል በትኩረት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።
የቀድሞ ግርማ ሞገሱን ከዘመናዊ አሰራር ጋር ያዋሃደው የቀፊራ ገበያ ለነጋዴዎችም ሆነ ለሸማቾች እንኳን ደስ አላችሁ!


