በድሬዳዋ አስተዳደር በኮሪደር ልማት የታደሰውና ለበርካታ ሺህ ዜጎች የኑሮ መሰረት የሆነው ታሪካዊው የቀፊራ የገበያ ማዕከል በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል።

በ1939 ዓ.ም አሁን ያለውን ቅርፅ ይዞ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቀፊራ የገበያ ማዕከል፣ ለዘመናት ሲታይበት የነበረውን የፅዳት ጉድለት፣ የትራፊክ መጨናነቅና ህገ-ወጥ ንግድ ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ በኮሪደር ልማት ታድሶ ለምረቃ በቅቷል።

ማዕከሉ በዘመናዊ መልኩ መታደሱ ለሸማቾችና ለነጋዴዎች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ ባለፈ፣ ለከተማዋ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ማዕከሉ ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀረርጌ፣ ሶማሌ ክልልና እስከ ጅቡቲ ድረስ የግብርና ምርቶችን የሚያከፋፍል ቁልፍ የንግድ ማዕከል መሆኑን በምርቃቱ ወቅት ገልፀዋል።

ቀፊራ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም አሁን በተከናወነለት የማዘመንና የማደስ ስራ ለንግድ ስራ ምቹ መሆኑን ክቡር ከንቲባው ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ የቀፊራ ገበያ ማዕከል ለከተማዋ ነዋሪዎች “የእናት ጓዳ” ያህል ሰፊና አስፈላጊ ቢሆንም፣ በውስጡ የነበሩት የፅዳትና የተዘበራረቀ ንግድ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በኮሪደር ልማቱ እነዚህን ችግሮች መፍታት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የወረዳ 06 አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ቢፍቱ መሀመድ በበኩላቸው፣ ቀፊራ የገበያ ማዕከል ብቻ ሳይሆን የከተማዋ የቱሪዝም ሀብት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን የቱሪዝም ፋይዳውን ይበልጥ ለማጉላት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የከተማዋ ካቢኔ አባላትና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የቀፊራ የገበያ ስፍራ የከተማዋ ነዋሪዎች በየቀኑ አልያም በሳምንት ሳይረግጡት የማይውሉበትና ለበርካታ ሺህ ወገኖች የመተዳደሪያና የኑሮ መሰረት ሆኖ የሚቀጥል መሆኑ ተመላክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *