ታሪካዊው የቀፊራ የንግድ ማዕከል በዘመናዊ መልክ ታድሶ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል።

ታሪካዊው የቀፊራ የገበያ ሥፍራ በኮሪደር ልማት እድሳት እና ተጨማሪ የማሻሻያ ሥራዎች ተከናውኖለት በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል።

በዚህም በምርቃት መርሃ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የቀፊራ መታደስ ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባ ከድር አያይዘውም ይህ ፕሮጀክት የታሪክና የዘመናዊነት ውህደት የታየበት መሆኑን ገልፀው፤ የቀፊራን ነባር ማንነት ሳይቀይር ለነጋዴዎች ምቹና ከጸሐይና ከዝናብ የተከለለ የሥራ አካባቢን መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።

ይህም የድሬዳዋን ህዝብ የንግድ ባህል ከዘመናዊ የከተማ ገጽታ ጋር ያቆራኘ ተግባር መሆኑን ክቡር ከንቲባው አክለው ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ግንባታው የከተማዋን የታሪክ አሻራ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎበት የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

አቶ ኢብራሂም እንደገለጹት፣ በማዕከሉ የተገነቡት ዘመናዊ መጠለያዎች፣ የተዘረጋው ጥራት ያለው የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት እና በምሽት አካባቢውን የሚያደምቁ መብራቶች ማዕከሉን ለንግድ ሥራ ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ አድርገውታል።

የክፍት ገበያ ሥፍራው እድሳት መጠናቀቅም ነጋዴዎች ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረውን የሥራ ቦታ ዝርክርክነት በማስቀረት ጸዳ ባለና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የንግድ ልውውጥ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል ሲሉ አቶ ኢብራሂም ገልፀዋል።

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ አካል የሆነው ይህ ፕሮጀክት የቀፊራን ታሪካዊ ክብር በመመለስ፣ አካባቢውን ከቆሻሻና ከዝርክርክነት ገጽታ አላቆ ለከተማዋ ዘመናዊነትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ አቅም ሆኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *