በድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጅሃር የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በሐረሪ ክልል ያደረገውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከሪያ ጉብኝት በስኬት አጠናቋል።
ጉብኝቱ በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች መካከል ያለውን ታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስር ከማጠናከር ባለፈ፣ በጋራ የልማትና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጅሃር በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ “ድሬዳዋና ሐረሪ በጂኦግራፊ ብቻ ሳይሆን በታሪክ፣ በባህልና በደም የተሳሰሩ ወንድማማች ሕዝቦች የሚኖሩባቸው ከተሞች ናቸው” ብለዋል።
ከንቲባ ከድር አክለውም ይህ ጉብኝትና የተከናወኑት ስፖርታዊ ውድድሮች የሁለቱን አካባቢዎች ሕዝባዊ ወዳጅነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ጉብኝቱ ሁለት ግዙፍ ስትራቴጂካዊ ግቦችን አንግቦ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ኃላፊው እንደገለጹት፤ የመጀመሪያው ግብ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሁለቱ አካባቢዎች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ይበልጥ ማጠናከር ሲሆን፤ የጋራ የፖለቲካ ንቅናቄና የሕዝብ ንቅናቄ ሥራዎችን በልዩ ትኩረት ማከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁለተኛው ግብ ደግሞ ስፖርታዊ ውድድሮችን ከመዝናኛነት ባለፈ፣ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል፣ የልማትና የማኅበራዊ ትስስር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ኢብራሂም አያይዘውም “ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው ባሻገር በጋራ ልማትና በዘላቂ ሰላም ዙሪያ የምንመክርባቸው መድረኮች ቀጣይነት ይኖራቸዋል” ብለዋል።
ልዑኩ በቆይታው የሐረሪ ክልልን ገጽታ የቀየረውን የኮሪደር ልማት ሥራዎች የጎበኘ ሲሆን፣ ይህም የልምድ ልውውጥን ለማሳደግና የብልፅግና ጉዞን በተግባር ለማሳየት ትልቅ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።


