ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ85ኛው የዐርበኞች ድል በዓል የአደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለ85ኛው የጀግኖች ዐርበኞች በዓል አደረሳችሁ
ሚያዝያ 27 ቀን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ዐርበኞች የፋሽስትን ወረራ የቀለበሱበት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ ያስከበሩበት በዓል ነው።
ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ያለ ዋጋ የሚከፈል ከራስ ወዳድነት የነጻ መሥዋዕትነት ነው።
ዓላማውም ሀገርን እና ሕዝብን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው። ለግል ወይም ለቡድን በተለየ የሚገኝ ነገር የለውም። ለሀገር ከሚገኘው ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር ከሚደርስ የዜጋ ድርሻ በቀር።
እናት እና አባት ዐርበኞች ከፋሺስት ጋር የተዋጉት ለሀገር እና ለወገን ብለው ነው። በግል ጥቅም ለማግኘትማ ከዐርበኝነት ይልቅ ባንዳነት አቋራጭ ነበር። ግን አላደረጉትም።
የዐርበኝነት ትግሉ ከሦስት ጠላቶች ጋር የተደረገ ነበር። ከራስ ፍላጎት፣ ከባንዳ እና ከወራሪ ፋሺስት ጋር። ዐርበኝነት የራስን ጥቅም ለሀገር ጥቅም ሲባል መተው ነው። ዐርበኝነት የግል ክብርን፣ የግል ሥልጣንን እና የግል ጥቅምን መሠዋት ነው። ይህንን ለመቀበል ከጠላት በፊት ራስን ማሸነፍ ይጠይቃል።
ባንዳዎች ማለት ራሳቸውን ማሸነፍ ያቃታቸው ናቸው። የግል ጥቅምን እና ክብርን ማሸነፍ ሲያቅታቸው የሀገራቸውን ክብር እና ጥቅም ይሸጣሉ። ባንዳነት ማለት ሀገርን ለራስ ጥቅም በመሸጥ የሚከናነቡት የውርደት ካባ ነው። ዐርበኞች ከባንዳዎች ጋር ታግለዋል። ባንዳዎች በአንድ በኩል ሀገራችሁን ሽጣችሁ እንደኛ በግል ተጠቀሙ ይሏቸዋል። በሌላ በኩል መንገድ እየመሩ ወራሪውን ያመጡባቸዋል። ያም አልሆን ሲላቸው ሕዝቡን በሐሰተኛ ወሬ ልቡን ይሰልቡባቸዋል።
ዛሬም ሦስቱም ጠላቶች አሉ። መልክና ስም ብቻ ቀይረዋል። በሌላም በኩል ዛሬም በየመስኩ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ዐርበኞች አሉ።
የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ብሔራዊ ዐርበኞችን ይፈልጋል። የራስ ፍላጎትን፣ ባንዳነትን እና ወራሪን እምቢ የሚል ዐርበኝነት።
የኢንዱስትሪ ዐርበኞች፣ የግብርና ዐርበኞች፣ የጸጥታ ዐርበኞች፣ የፖለቲካ ዐርበኞች፣ የንግድ ዐርበኞች፣ የዲፕሎማሲ ዐርበኞች፣ የመንግሥት አገልጋይ ዐርበኞች፣ የሕክምና ዐርበኞች፣ የትምህርት ዐርበኞች፣ ወዘተ. ያስፈልጉናል።
ይህንን በዓል የምናከብረው የየራሳችንን የዐርበኝነት ደረጃ በመገምገም ነው። ለኢትዮጵያ ምን ያህል ዐርበኞች ነን?
ዛሬም የግል ፍላጎት የሚያሸንፋቸው ደካሞች አሉ። ሀገርን አፍርሰው የግል ቤት መሥራት የሚመኙ። ትልቁን መርከብ አፍርሰው ትንንሽ ታንኳዎችን ለመሸጥ የሚመኙ። ለቅንጥብጣቢ ነገር ውርደትን ለመሸከም የማይሰቀቁ።
ዛሬም ወራሪዎች አሉ። በአካል ሀገርን ለመውረር ካሰፈሰፉት በተጨማሪ ድህነት፣ ኋላቀርነት እና ሌብነት የሚባሉ እንደ ሰርዶ ሀገርን ወርረው ሽባ የሚያደርጉ ጠላቶች አሉ። ሀገርን ለባዳ ከሚሸጡት ባንዳዎች እኩል፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚሸጡ ባንዳዎች አሉ። አገልግሎትን እና የሕዝብን ሀብት የሚሸቅጡ ባንዳዎች አሉ።
ብሔራዊ ዐርበኝነት ማለት እነዚህን ሦስት ጠላቶች ታግሎ ማሸነፍ ማለት ነው። ዛሬ የምናየውን የኢትዮጵያ ለውጥና ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለው ብሔራዊ ዐርበኞች በየአካባቢው በመኖራቸው ነው። ብሔራዊ ዐርበኞች ሦስቱን ጠላቶች እያሸነፉ ቢሆንም ገና ሙሉ በሙሉ ድልን አልተቀዳጁም።
ድሉ እንደ ሚያዝያ 27 የሚታወጀው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ስትሆን ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ከሚገኙ ኃያል ሀገሮች አንዷ ስትሆን ነው።
ይሄንን ድል እውን ለማድረግ ኢትዮጵያን የሚወዱ የኢትዮጵያ ዐርበኞች ሁሉ እንዲነሡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 27፣ 2018 ዓ.ም


