የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ለ85ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል

መላው የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና የሀገራችን ሕዝቦች፤ እንኳን ለ85ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!

ይህ ታላቅ የድል በዓል አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ እንዲሁም በየዘመናቱ የነበሩ ወጣቶቻችንና እህቶቻችን ለታላቋ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት የከፈሉትን ወደር የሌለው መስዋዕትነት የምንዘክርበት ታሪካዊ ዕለት ነው።

አርበኞቻችን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው በጋራ በመቆማቸው ሀገርን ከወራሪ ማዳን እንደቻሉ ሁሉ፣ ዛሬም እኛ በመደመር እሳቤ ይበልጥ አንድ ሆነን ተጋምደን፣ ካሉን ጠንካራ እሴቶቻችን ጋር አዳዲስ የልማት ስራዎችን በማቀናጀት የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግናን ማፋጠን ይጠበቅብናል።

የዛሬው ትውልድ አርበኝነት ድህነትን በስራና በትጋት ማሸነፍ፣ እኛን ከሚከፋፍሉን ሀሰተኞችና ሴረኞች በመራቅ አንድነታችንን ይበልጥ አጠናክረን፣ እጅ ለእጅ በመያያዝ ልማታችንን ማፋጠንና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው።

“ከለውጥ ማግስት ወዲህ በአስተዳደራችን የጀመርናቸው የተለያዩ የልማት ስራዎች፣ ሰፋፊ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም አያሌ ሜጋ ፕሮጀክቶች፤ በሀገር ደረጃም ካሉ ግዙፍ የልማት ውጥኖች ጋር ተቀናጅተው ውጤት እንዲያመጡ በትጋት እየሰራን እንገኛለን።

እነዚህን ታላላቅ ሀገራዊ ትልሞች ‘ጀምሮ ማቆም’ ሳይሆን ‘ጀምሮ መጨረስን’ በተግባር በማረጋገጥ፣ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ በመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘንድ እየታየ ያለው ላቅ ያለ ትብብር፣ ድጋፍና ጠንካራ ህብረት በርግጥም የዘመናችን አስደናቂ የአርበኝነት መገለጫ ነው።

ያለፈውን የዘመናት ታሪኮቻችንን እያከበርን፣ ለነገዋ እድገትና ብልጽግናችን ጠንክረንና ተግተን በመስራት፣ አንድነታችንን፣ ፍቅራችንንና ህብረታችንን ይበልጥ በማላቅ እና ሁላችንም በጋራ በመቆም በሁሉም ዘርፎቻችን ውጤታማና ፍሬያማ ስራዎችን በማከናወን ድሬዳዋችንንና ሀገራችንንም ወደ ቀድሞው ከፍታዋ ላይ ማድረስ እንችላለን፤ በማድረስ ላይም እንገኛለን።

በባለፉት በርካታ ዘመናት አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በከፈሉት መራር ዋጋና መስዋዕትነት፣ ብሎም ለእኛ ልጆቻቸው ሲሉ ከትግል ሜዳ ወድቀው በደማቸውና በአጥንታቸው ያስከበሩትን ሀገራችንን ዛሬ ላይ እኛ በላቀ ስራዎቻችን፣ በተጋመደ አብሮነታችንና አንድነታችን እነሆ በእጅጉን ልናጸናት ይገባል።

ይህ የድል በዓል ለድሬዳዋ አስተዳደራችንና ለመላው ሀገራችን ዘላቂ ሰላምን፣ ብልጽግናንና የላቀ እድገትን ይዞ እንዲመጣ ልባዊ ምኞቴ ነው።

ክብርና ሞገስ ለጀግኖች አርበኞቻችን!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

መልካም በዓል!!!

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ

አቶ ከድር ጁሃር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *