የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ወርቅነህ ለ85ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

============

መላው የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና የሀገራችን ሕዝቦች፤ እንኳን ለ85ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! እንኳን አደረሰን! የአርበኞች የድል በዓል፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና የሆኑት አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ የግፍ ወረራን በፅናትና ባልተገደበ መስዋዕትነት ድል ያደረጉበት የታሪክ አሻራ ነው።

አርበኞቻችን ያኔ በዱር በገደሉ የተዋደቁት ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ብቻ ሳይሆን፣ እኛ ዛሬ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንራመድባት፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረች ሀገር እንድትኖረን በማለም ነው።

ዛሬ ላይ ሆነን ይህን ታላቅ የድል ቀን ስናከብር፣ ዕለቱ ታሪክን ለማስታወስ ብቻ ሳይሆን አባቶቻችን በደምና በአጥንት ያቆዩልንን ነፃነት በመደመር እሳቤ አጽንተን፣ ለዘመኑ በሚመጥን የልማት ስኬት አጅበን ለቀጣዩ ትውልድ የምትረከብ ታላቅ ሀገር ለመገንባት ቃል የምንገባበት የታሪክ መድረክ ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመደመር እሳቤ መመራታችን በድሬዳዋ አስተዳደርም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ የሆኑ የልማት ድሎችን እንድናስመዘግብ አስችሎናል።

በተለይም በድሬዳዋ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የታዩት ግዙፍ የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ መናኸሪያነታችንን ያረጋገጠው የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና፣ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ያሳደገው የሌማት ትሩፋትና ዘመናዊ የግብርና ስራዎች፣ የንግድ ስርአቱን ያዘመኑ የገበያ ማዕከላት ግንባታ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች የተፈጠሩ ሰፊ የሥራ ዕድሎች፣ እንዲሁም የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ሁሉ በአብሮነት ሰርተን ያገኘናቸው የጋራ ድሎቻችን ናቸው።

እነዚህ ስኬቶች በአንድነትና በመደመር መንፈስ ስንቆም፣ የማይታለፉ የሚመስሉ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የልማት ግቦቻችንን ማሳካት እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ናቸው። ያኔ አርበኞቻችን ለሀገራችን ሉዓላዊነት በጋራ መቆማቸው ለዛሬው የለውጥ ጉዟችን ትልቁ ስንቅ ነው።

እውነተኛ አርበኝነት ዛሬ ላይ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን፣ የሥራ ፈጠራና የልማት ስራዎችን በላቀ ጽናት በማስቀጠል፣ ሰላምን ማፅናት፣ በስራ ትጋት ውጤት ማምጣትና ለጋራ እድገት በቁርጠኝነት መቆም ነው።

ስለሆነም የድሬዳዋ ህዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ አብሮነትን የሁልጊዜ መገለጫው በማድረግ፣ እየተከናወኑ ያሉ የልማትና የሰላም ስራዎችን በባለቤትነት በመደገፍ ታሪካዊ አርበኝነቱን እንዲያጸና ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በድጋሚ እንኳን ለ85ኛው የአርበኞች ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና አንድነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

አቶ ብሩክ ወርቅነህ

የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ

ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *