ብልፅግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር በማረጋገጥ ውጤት ተኮርነቱን በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑ ተገለፀ::

“ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ቃል፣ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የሻይ ቡና መርሃ ግብር በድሬዳዋ አስተዳደር በወረዳ 03 ተካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ወርቅነህ፤ ብልፅግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈፀም፣ ለቃሉ የታመነ እና በስራው ውጤት ተኮርነቱን በተጨባጭ ያስመሰከረ ፓርቲ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፓርቲው በርካታ ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች አመርቂ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉን ኃላፊው በዝርዝር አብራርተዋል።

አቶ ብሩክ አያይዘውም፣ ፓርቲው ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በስኬት ማጠናቀቁን ጠቁመው፤ በተለይም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩት የኮሪደር ልማትና የከተማ ውበት ስራዎች ከተማን ከማስዋብ ባለፈ፣ የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ የቀየሩና ኢትዮጵያን የቱሪስት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዲፕሎማሲው ረገድም ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት እንዲጨምርና ሀገራዊ ጥቅሟ እንዲከበር ብልፅግና ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን አቶ ብሩክ አክለዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደርም በለውጡ ዓመታት ሰላምን በማፅናት፣ በኢንዱስትሪ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በሰው ተኮር ተግባራት እንዲሁም በከተማ ልማት ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የጠቀሱት አቶ ብሩክ፤ በወረዳ 03 የተሰሩ የልማት ስራዎችም የማህበረሰቡን ኑሮ በተጨባጭ በማሻሻል ረገድ ትልቅ አሻራ ማሳረፋቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የተጀመሩ ግዙፍ ስራዎችንና ሰው ተኮር ልማቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የብልፅግና ፓርቲ ምልክት የሆነውን “የስንዴ ነዶን” መምረጥ ይገባል ሲሉ አቶ ብሩክ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ በአብሮነትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባው ኃላፊው ገልፀዋል።

የወረዳ 03 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምትኩ ሁነኛው በበኩላቸው፣ “የስንዴ ነዶ” የአብሮነት፣ የጥንካሬ እና የአንድነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ምትኩ አያይዘውም ህብረብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠልና ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር ለማድረግ የስንዴ ነዶን መምረጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የስንዴ ነዶን መምረጥ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የመርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች ናቸው።

ወረዳውን ወክለው ለአስተዳደሩ ምክር ቤት የሚወዳደሩ የብልፅግና ፓርቲ እጩዎችን ለነዋሪው በማስተዋወቅ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *