በድሬዳዋ አስተዳደር እና በሶማሊ ክልል መካከል ያለውን የንግድና የማህበራዊ ትስስር ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ የሚጠበቀው የድሬዳዋ-ሺኒሌ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት ተጠናቆ በይፋ ተመረቀ።
ለዚህ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ታውቋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደን ፋራህ እንዲሁም የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ በጋራ በመሆን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገውታል።
ይህ 10.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ፕሮጀክት፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ከሶማሊ ክልል ሲቲ ዞን ሺኒሌ ከተማ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ስትራቴጂካዊ መስመር ነው።
ቀደም ሲል በጠጠር ደረጃ የነበረው ይህ መንገድ፣ አሁን ላይ ደረጃውን በጠበቀ የአስፓልት ኮንክሪት መገንባቱ የአካባቢውን የትራንስፖርት ፍሰት ከማሳለጡም በላይ፣ በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይታመናል።
በምረቃው ወቅት እንደተገለጸው፣ መንገዱ ለነዋሪዎች ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ የንግድ ልውውጥን በማቀላጠፍ ለቀጠናው ልማት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።


