የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ አመራሮችና አባላት የማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
በዚሁ የማዕረግ ማልበስ መርሃ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር፤ በዛሬው ዕለት የማዕረግ ዕድገት ያገኙ የፖሊስ ኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ተነሳሽነት በበለጠ በመሥራት፣ ነዋሪውን ማኅበረሰብ በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ክቡር ከንቲባው አክለውም፣ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን በመላው አገሪቱ ለሚካሄደው 7ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።
የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው፤ የድሬዳዋ ፖሊስ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ካከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች መካከል በተቋሙ ውስጥ የሚገኘውን የሰው ኃይል በሥልጠና፣ በክህሎት፣ በአእምሯዊና በአካላዊ ብቃት ማጠናከር ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
በተሠሩት የእነዚህ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችም በአስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታን ከማስከበር ባለፈ፣ የድሬዳዋ ፖሊስን ገጽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ መገንባት መቻሉን አስታውቀዋል።
በመርሃ-ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ የማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን፣ የፖሊስ ኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት በሁርሶ በነበራቸው የሥልጠና ቆይታ ወቅት ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት ከዕለቱ የክብር እንግዳ እጅ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።


