የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 የሚካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢቢሲ የሰጡ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ መራጩ ሕዝብ ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት ያግዛል ያለውን ለመምረጥ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ወጣት ዳግማዊት አዲሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የመምረጥ ዕድል በማግኘቷ ቀኑን በጉጉት እየጠበቀችው መሆኗን ገልጻ፣ ለመምረጥ መዘጋጀቷን ተናግራለች።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ሙፈርያት ታዬ ለመምረጥ መዘጋጀቷን በመግለጽ፣ ሁሉም አካል ጉዳተኞች ድምፃቸውን በንቃት መስጠት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርባለች።
ነዋሪዎቹ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን ሲተላለፉ የነበሩትን የፓርቲዎች ክርክሮችና የምረጡኝ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ መከታተላቸውን ጠቁመው፣ ይህም ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ያሉትን የፖሊሲ አማራጮች በጥንቃቄ ለመለየት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
እያንዳንዷ የድምፅ መስጫ ካርድ ያላት ሀገራዊ ዋጋ በቀላሉ የሚገመት ባለመሆኑ፣ ካርድ የወሰዱ ዜጎች ሁሉ ሰኞ ዕለት በነቂስ በመውጣት ታሪካዊ ውሳኔ ማሳረፍ እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


