የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገለጹ

የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ የዜግነት መብታቸውን ለመጠቀምና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር በሂደቱ ላይ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

የወሰዱትን የመምረጫ ካርድ በጥንቃቄ በመያዝ ቀኑን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ያመላከቱት ነዋሪዎቹ፤ የምርጫው ሂደት ሥነ-ሥርዓትና በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የመምረጥ መብት ያገኙ ወጣቶች፣ ሴቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በምርጫው ሂደት ላይ ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ ማንኛውም ካርድ የወሰደ ዜጋ መብቱን ሊጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

እያንዳንዷ የድምፅ መስጫ ካርድ ለሀገር የወደፊት ጉዞ ትልቅ ዋጋ ያላት በመሆኑ፣ የምርጫ ካርድ የወሰዱ የድሬዳዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ በዕለቱ በጥዋቱ ወደየምርጫ ጣቢያዎቻቸው በመሄድ በሰላማዊ መንገድ ድምፃቸውን እንዲሰጡ እና አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *