በድሬዳዋ አስተዳደር ለሰባተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሚያገለግሉ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማሰራጨት ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን መሀመድ ለድሬዳዋ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለምርጫው የሚያገለግሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ ሳጥኖች እና መከለያዎች በአራቱም የገጠር ክላስተሮች በሚገኙ 130 የምርጫ ጣቢያዎች እየተከፋፈሉ ይገኛሉ።
በክላስተሮቹ ሥር ባሉ 38 የገጠር ቀበሌዎች ቁሳቁሱን በአግባቡ ለማከፋፈል አስፈላጊው የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት አቅርቦት መሟላቱን ኃላፊው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቁሳቁሶችን በአስተማማኝ ሁኔታ አጅበው እስከ ምርጫ ጣቢያው የሚያደርሱ የፀጥታ ኃይሎች በአስተዳደሩ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ተመድበው ወደ ሥራ ገብተዋል።
ከትናንት ግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎችን የማዘጋጀት፣ ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ አዳራሾችን ምቹ የማድረግ እና የድንኳን ተከላ ሥራዎች በምርጫ አስፈጻሚዎች አማካኝነት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ዝግጁ ሆነዋል።
የምርጫ ቁሳቁሶችን እስከ ነገ ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተቀሩት የከተማ ምርጫ ጣቢያዎች አሰራጭቶ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ ዚያድ ገልጸዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የምርጫው «የጥሞና ወቅት» ላይ በመደረሱ፤ ማንኛውንም ዓይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ መሆኑንና ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና ዕጩዎች ይህንን አውቀው ተግባራዊ እያደረጉት እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን፤ በድሬዳዋ አስተዳደር በአጠቃላይ 297 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ።


