የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ ማህበር ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊሰጥ ነው

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፊታችን ሰኞ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ ማህበር አስታወቀ።

መራጩ ማህበረሰብ ያለምንም እንግልትና የትራንስፖርት ችግር ሳይገጥመው ድምጹን መስጠት እንዲችል ማህበሩ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አሽከርካሪዎች ገልጸዋል።

የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት ቃልኪዳን ፀሐይ እንደገለፀው፣ ማህበሩ በአጠቃላይ 500 አባላት ያሉት ሲሆን ሁሉም አባላት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውንና በዕለቱ ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ተናግሯል።

ከሀገር አቀፍ የዜግነት ግዴታቸው ጎን ለጎን ማህበረሰቡን በበጎ አድራጎት ለማገልገል መነሳሳታቸውን የገለጹት አሽከርካሪዎች፤ ለወጣቶች ተጠቃሚነት እንዲሁም ለሀገራችን ሰላምና ዕድገት ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት እንደሚመርጡ ለኢቢሲ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

ሀገር ስትኖርና ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ መስራትና መኖር እንደሚቻል የጠቀሱት አሽከርካሪዎቹ፣ ምርጫው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣትነት ሚናቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *