ሰባተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ ዛሬ በዋዜማው የመላው ድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች በዲሞክራሲ፣ በሰላም እና በነፃነት ለመምረጥ ሙሉ በሙሉ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ህዝቡ የዜግነት ኃላፊነቱን ለመወጣት እና የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ለመወሰን ነገ ጠዋት 12:00 ሰዓት ላይ የምርጫ ጣቢያዎች የሚከፈቱበትን ታሪካዊ ቅጽበት በከፍተኛ መነቃቃት እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መብታቸውን በነፃነት ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል።
ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት፤ ነገ የሚሰጡት እያንዳንዱ ድምፅ ለዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ የነገውን ማለዳ በታላቅ የተስፋ ስሜት እየተጠባበቁት መሆናቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላው አስተዳደሩ ፍጹም የተረጋጋና ሰላማዊ የዋዜማ ድባብ የሰፈነ ሲሆን፣ ህዝቡም ነገ ማለዳ 12:00 ሰዓት ላይ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የዲሞክራሲ ተሳትፎውን በተግባር ለማሳየት በንቃት እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።


