በህዝብና በሀገር ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ሁነቶች መካከል ምርጫ አንዱ ነው። ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ እስከ ምርጫው እለት ድረስ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር የወረዳ 5 እና የወረዳ 6 ነዋሪዎች ገለፁ።
የምርጫ ካርዴን በወቅቱ ወስጃለሁ፤ የዘንድሮን ምርጫ ለመምረጥ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነኝ። ድምፅ መስጠት መብቴ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታዬም በመሆኑ፣ ነገ ማለዳ ተገኝቼ የምፈልገውን ዕጩ እመርጣለሁም ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡን መራጮች እንደተናገሩት፣ ካርድ መውሰድ የዜግነት ግዴታን ለመወጣት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲሆን፣ በዕለቱ ተገኝቶ ድምፅ መስጠት ደግሞ የሀገርን መረጋጋት እና ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በዘመናዊ መልክ በተከናወነው የዲጂታል መራጮች ምዝገባ ስርዓት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ በመሆኑ የዘንድሮ ምርጫ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡን የወረዳ 5 እና የወረዳ 6 ነዋሪዎች ድምፃቸውን ለመስጠት በጉጉት መጠበቃቸው፣ በሀገሪቱ የሚነሱ ማናቸውም የፖለቲካ ጥያቄዎች ወይም የሥልጣን ለውጦች በሰላማዊ መንገድ፣ በምርጫ ሳጥን ብቻ እንዲወሰኑ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ሌሎች አስተያየታቸውን የሰጡ የንግድ ማኅበረሰብ አካላት ደግሞ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆንና የኢኮኖሚ መረጋጋትን የሚያመጡ ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የእኛ ትልቅ ምኞት ሰላም ነው፤ ሰላም ሲኖር ነው መሥራት የምንችለው። ስለዚህ የምንመርጠው አካል ለሀገር ሰላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሔ እንዲያመጣ እንጠብቃለን ሲሉ አክለዋል።


