የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
1ኛ:- ካቢኔው በቀዳሚነት የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ፕላን ሥራዎች ላይ በመወያየት ውሳኔ አስተላልፏል።
የከተማ ፕላን ሥራዎች የድሬዳዋን ፈጣን ዕድገት በስልታዊ መንገድ ለመምራት ከፍተኛ ሚና አላቸው። የመኖሪያና የንግድ ቀጠናዎችን በዘመናዊ አሠራር በመለየት ለቀጣይ መሠረተ ልማት፣ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት እና ለከተማዋ ውበት ምቹና ዘላቂ መሠረት ይፈጥራሉ።
2ኛ:- ካቢኔው በመቀጠልም አዲሱ የድሬዳዋ ዘመናዊ ቄራ የራሱ የሆነ የውሃ አቅርቦት እንዲኖረው በአማካሪ ድርጅት በቀረበው የጥናት ሰነድ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
የድሬዳዋ ዘመናዊ ቄራ ራሱን የቻለ የውሃ አቅርቦት ማግኘቱ ተቋሙ ያለምንም መቆራረጥ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ እንዲሠራ ያደርጋል። ይህም ለከተማው ማህበረሰብ የሚቀርበው የሥጋ ምርት ሁልጊዜም በከፍተኛ ንጽሕና እና በጤናማ ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንዲደርስ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው።
3ኛ:- በመቀጠልም ካቢኔው፤ ከህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ሰፊ ውይይት አካሂዷል። በተለይም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የህዝቡን አንኳር ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመወያየት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በመጨረሻም ካቢኔው፤ በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ሌሎች ተያያዥ የልማት አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመወያየት ስብሰባውን አጠናቋል።


