የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግር እና ኒዩትሪሽን ንቅናቄ በድሬዳዋ አስተዳደር በይፋ መተግበር መጀመሩ ተበሰረ::

​የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት (ATI) ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በመተባበር ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚተገበር “የምግብ ሥርዓት ሽግግር ፍኖተ-ካርታ” ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አከናወነ።

ይህ ፍኖተ-ካርታ በአስተዳደሩ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖረውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግና የተመጣጠነ የምግብ ስርዓት እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

​የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዶ/ር ሰይፉ ታደሰ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት የፍኖተ-ካርታው ራዕይ በከተማም ሆነ በገጠር ሳይከፋፈል በድሬዳዋ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ የሚመገብ ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር ነው።

እንደ ​ዶ/ር ሰይፉ ገለጻ ፍኖተ-ካርታው እስከ ፈረንጆቹ 2030 በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሁሉም ሴክተሮች ላይ በተቀናጀ መልኩ የሚተገበር የረዥም ጊዜ ጥናት ውጤት ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ከተረጂነት ለመውጣትና ምንም ዓይነት የምግብ ድጋፍ ከውጪ ላለመቀበል የያዘችውን ብሔራዊ እቅድ ለማሳካት ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።

​በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን የክላስተር አስተባባሪ አቶ ደበሌ ደበላ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በፌዴራል ደረጃ የተዘጋጀውን ፍኖተ-ካርታ የድሬዳዋ አስተዳደር ወደ ራሱ ተጨባጭ ሁኔታ በመቅረጽና ተስማሚ በሆነ መልኩ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት ሃላፊዎች አቅርቦ ማጽደቁንና በመጪው በጀት ዓመት በቀጥታ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

​ቀደም ሲል እያንዳንዱ ሴክተር ተቋም በተናጠል በሚያከናውናቸው ስራዎች ምክንያት የሀገሪቱ የስርዓተ-ምግብ ችግር ሳይፈታ መቆየቱን እንደ ተግዳሮት ያነሱት አቶ ደበሌ፤ በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በጋራ እንዲሳተፉ መደረጉ ጊዜን፣ ገንዘብን እና ጉልበትን ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል።

​ በአሁኑ ወቅት የምግብ ሥርዓታችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ጫና ውስጥ እንደሚገኝ በመድረኩ ላይ በቀረበው ሪፖርት የተመላከተ ሲሆን ይህም በአካባቢያችን ባልተስተካከለ የዝናብ ስርጭትና በአርብቶ አደር ቀበሌዎች ላይ በሚከሰት ድርቅ ይገለፃል።

ከዚህ በተጨማሪም ፈጣን የከተማ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የምግብ ዋጋ መዋዠቅ ተግዳሮቶቹን ይበልጥ እንዳባባሱትም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

​የዚህ ፍኖተ-ካርታ ወደ ትግበራ መግባት ለከተማዋ ነዋሪዎችም ሆነ ለገጠር ቀበሌዎች የምግብና የምግብ ሥርዓት ፍላጎት ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ፤ ምርታማ፣ አካታች እና የማይበገር የምግብ ሥርዓት ለመገንባት የተያዘውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑም ከመድረኩ ተሳታፊዎች ተነስቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *