በወ/ሮ ፍሬአለም ሽባባው የተመራ የሚኒስቴሩ የልዑካን ቡድን በድሬዳዋ ከተማ በመገኘት ከአመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ሽማግሌዎች እና ከኢሳ ጎሳ መሪዎች ጋር ተወያዩ::

    በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬአለም ሽባባው የተመራ የልዑካን ቡድን በድሬዳዋ ከተማ ተገኝቶ የዞንና ወረዳ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ሽማግሌዎች፣ የኢሳ ጎሳ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል::
    የልዑካን ቡድኑ ከጥቂት ቀናት በፊት በአፋር ክልል በመገኘት በተመሳሳይ የማህበረሰብ እና አመራሮች ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
    በውይይቶቹ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚበጁ ገንቢ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡
    ወ/ሮ ፍሬአለም የተነሱ ምክረ ሀሳቦችንና መጠይቆችን ተቀብለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
    ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሁላችንም መተባበር አለብን ብለዋል::
    ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ ትልቅና ውብ ሀገር ናትግጭት ሲፈጠር በተረጋጋና በሰለጠነ መንገድ መወያየት ይገባል ሲሉም ገልጸዋል::
    ኃይል መጠቀም በአስቸኳይ መቆም አለበት፤ አመራሩም በስርዓት ለህግ መከበር መቆም አለበት ነው ያሉት፡፡
    አክለውም የወገኖቻችንን ጉዳት ልንቀብል አይገባም፤ ህጻናት የነገ የዚህች ሀገር ተስፋ ናቸውና ወደ ትምህርት ቤት መመለስ አለባቸው ብለዋል::
    እናቶች እንባቸው ሊታበስ ይገባል ያሉት ወ/ሮ ፍሬአለም ሽባባው ለማህበረሰቡ የሚያስፈልጉ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የመንገድ፣ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ በአፋጣኝ በጋራ መስራት አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::
    በመወያየትና በመደማማጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ህዝብን ባማከለ መልኩ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ያስፈልገናል ብለዋል::
    መንግስት በቀጣይነት የቀጠናው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል::
    በመጨረሻም የማህበረሰብ ተወካዮችን፥ የጎሳና የሃይማኖት መሪዎችን፥ አመራሩን እና በአጠቃላይ የውይቱን ተሳታፊዎችን አመስግነዋል፡፡
    ምንጭ ፡- (ኤፍ ቢ ሲ)