በድሬዳዋ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና ጥራታቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች ከየመደብሩ ተሰብስበው እንዲወገዱ ተደረገ::

    በድሬዳዋ አስተዳደር በተካሄደ ቁጥጥር የተሰበሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብ ነክ ሸቀጦችና ጥራታቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች እንዲወገዱ ተደረገ።
    የማስወገዱ ሥራ ዛሬ በተከናወነበት ወቅት በአስተዳደሩ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር የስራ ሂደት ባለቤት ሲስተር ሰሪዶ ኡመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በማቃጠል የተወገዱት ምግብ ነክ ሸቆጦች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ናቸው።
    እነዚህ በከተማው ከሚገኙ 340 ሱቆች የተሰበሰቡ ምግብ ነክ ሸቆጦች የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ሓላፊዋ አመልክተዋል።
    በጥቆማ፣ በድንገተኛ ፍተሻና ከቀበሌ የጤና ዘርፎች ጋር በመቀናጀት ለ20 ቀናት በተካሄደ የቁጥጥር ሥራ ምርቶቹን በመሰብሰብ ማስወገድ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
    ከተወገዱት መካከል የታሸጉ ብስኩቶች፣ ጁሶች፣ ለህጻናት በተጨማሪ ምግብነት የሚያገለግሉ የምግብ ምርቶችና ወተት ይገኙበታል፡፡
    የተወገዱ ምግብ ነክ ሸቀጦች ጥቅም ላይ ቢውሉ በጤና ላይ እስከ ሞት ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ሲስተር ሰሪዶ ገልጸዋል፡፡
    የንግዱ ማህበረሰብ በፍተሻ ወቅት ያሳየው ትብብር አበረታች መሆኑን ጠቅሰው መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚጠናከር ጠቁመዋል፡፡
    በትምህርት የማይመለሰውና ጉዳት ለማድረስ የሚንቀሳቀሰው አካል ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል፡፡
    በተመሳሳይ ጥራት የሌለው አልኮልና ሳኒታይዘር ሲሸጡ የተደረሰባቸው አራት የመድኃኒት መሻጫ መደብሮች ታሽገው በመደብሮቹ የነበሩ ሕገ-ወጥ መድኃኒቶችን በመለየት እንዲወገዱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
    በአወጋገዱ ሥነ-ሥርዓት የተገኙት ከህዝብ የተወከሉ ታዛቢ አቶ ዮሴፍ ዘሪሁን በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምግቦችና መድኃኒቶች እንዳይጠቀም መክረዋል፡፡
    የንግዱ ማህበረሰብ አባላትም የነዋሪውን ጤና የሚጎዱ ሸቀጦችን ለማስወገድ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
    ሌላው ታዛቢ አቶ ቶማስ እምቢበል በበኩላቸው ወጣቱ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሕገ-ወጥ መድኃኒትና ሸቀጥ የሚሸጡ ግለሰቦችና ድርጅቶችን በማጋለጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
    የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የጀመራቸውን የቁጥጥር ሥራዎች እንዲያጠናክርም የህዝብ ታዛቢዎቹ አሳስበዋል፡፡
    ምንጭ ፡- EBC