በድሬዳዋ አስተዳደር የጤና ባለሙያዎች እና የሙያ ማህበራት ተወካዮች የተሳተፉበት የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ቢሮ የሰዉ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሀቢብ በጤናው የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች በየጊዜዉ የዘርፉ ሙያ ከሚተገበሩ አዳዲስ አሰራሮችና ግብዓቶች ጋር እራሳቸዉን ማብቃት አለባቸዉ ብለዋል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በሀገራቀፍ ደረጃ በተቀመጠው የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ፕሮግራም በመሆኑ በዚህ ፕሮግራም መሰረት ማንኛዉም የጤና ባለሙያ በዓመት ለ30 ሰዓት ወይም 30 ነጥብ የሙያ ማሻሻያ መዉሰድ እንዳለባቸው ያስቀምጣል በማለት በዚሁ መሰረት በየጊዜዉ ከሚፈጠሩ የጤናዉ ዘርፍ ግብዓቶች እና አሰራሮች ዙሪያ እራሳቸዉን ማብቃት እንዳለባቸዉ አቶ መሀመድ ገልፀዋል ፡፡
የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ፕሮግራምና የዘርፉ የሙያ ምዝገባ ፍቃድ የሚሰጣቸው ሲሆን ይህም በፈለጉበት ክልልና ተቋም ተቀጥረው መስራት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑንና የጤና ባለሙያዎች የሙያ ፈቃድ ለመግኘት ይህ ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ወሳኝ መሆኑም በዚሁ መድረክ ላይ ተገልፆዋል፡፡


