ስድስተኛው ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር በድሬዳዋ አስተዳደር እንዲካሄድ ለማስቻል የፀጥታ አካላት በምርጫ የፀጥታ እቅድ ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡

    በ2013 ዓ.ም ስድስተኛው ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫን አስመልክቶ የጸጥታ እቅድ ውይይቱን የከፈቱት የድሬዳዋ አስተደደር ም/ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ምርጫው በአስተዳደራችን ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ስራቸውን በሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
    የፍትህ አካላት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ በመሆን ስራቸውን ማከናወን አለባቸው ያሉት ም/ከንቲባ አህመድ ለዚህም ከወዲሁ የፍትህ አካላት እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
    በውይይት መድረኩ የ2013 ዓ.ም የምርጫ ማስፈጸሚያ እቅድ በኢ/ር አንተነህ ረፌራ የቀረበ ሲሆን በዚህ እቅድ ላይ ቅድመ ምርጫ፤የምርጫው እለት እና ድህረ ምርጫ የፍትህ አላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ተብራርቷል፡፡
    በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ጸጥታ እና ህግ ጉዳዬች ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙሳ ጠሀ እንደገለጹት የጸጥታ አካላቱ በ2013 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቅሰው ሁሉም የጸጥታ አካላት የየራሱን እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
    በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የድሬዳዋ ፖሊስ ፤የፌደራል እና የመከላከያ እንዲሁም የቀበሌ የጸጥታ ሃላፊዎች ተገኝተውበታል፡፡
    ምንጭ ፡ ድሬ ፖሊስ