ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ለማህበረሰቡ አገልግሎት ሰጪ ንድፈ ሀሳቦችን መስራት መጀመሩን አስታወቀ።

    ለማህበረሰቡ አገልግሎት ሰጪ የመጀመሪያ ዙር የንድፈ ሀሳቦች መገምገሚያ ወርክሾፕ በዛሬው እለት በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ተካሄደ፡፡
    ዩኒቨርስቲው ካሉት ተልዕኮዎች አንዱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማገልገል ነው ያሉት የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዩች ምክትል ፕሪዘዳንትና የፕሪዘዳንቷ ተወካይ ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አቀፍና ችግር ፈቺ ንድፈ ሃሳቦችን ለመስራት የበጀት ችግር እንዳይገጥም በቂ በጀት በመበጀት ወደ ስራ መገባቱን በመግለፅ በዛሬው እለት ከሚቀርቡት አስራ አንድ ንድፈ ሀሳቦች አራቱ ተመርጠው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለመግባት መታቀዱንም ገልፀዋል ፡፡
    ደ/ር መገርሳ አክለውም ከአስተዳደሩ ጋር ቀደም ሲልም በመቀናጀት አብረው እንደሚሰሩ በመጠቆም በቀጣይም በአስተዳደሩ ባሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችና በምርምር ስራዎች የበለጠ አጠናክረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
    በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሪዘዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በንድፈ ሀሳቡ ወርክሾፕ ላይ እንደተናገሩት ቀደም ባሉት አመታት ዩኒቨርስቲው ከማህበረሰቡ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባለመኖሩ ክፍተቶች እንደነበሩ በመግለፅ ለቀጣይ ስራዎቻቸው ያሉትን ችግሮች በመፈተሽ ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ ንድፈ ሀሳቦችን በመስራት ማህበረሰቡን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ንድፈ ሀሳቦችን ለመስራት ወደ ትግበራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
    ደ/ር ሰለሞን ከዚህም ጋር አያይዘው ቀደም ሲል ከማህበረሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ቅድሚያ ሊሰጦቸው ይገባል ያላቸውን ተግባራት ቅድሚያ በመስጠት ወደ ጥናትና ምርምር መገባቱን ገልፀወዋል፡፡
    በዩኒቨርስቲው መምህር እና የንድፈ ሀሳብ አቅራቢ አቶ ቢኒያም አሰፋ ባቀረበው ንድፈ ሀሳብ የድሬደዋ ውበቷን የሚያጎላና ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር የአውቶቢስ መጠበቂያ ፣ የሱቅና የሊስትሮ ጫማ መጥረጊያ ያለው እንዲሁም የድሬደዋ አየር ንብረቷ ሙቀታማ በመሆኑ የአየር ማቀዝቀዣ ያለው ንድፈ ሃሳብ ይዞ መቅረቡንም ገልፃል፡፡