ተቋሙ በሁሉም ቅርንጫፎቹ የኮር ባንኪንግን በመጠቀም ፈጣንና ዘመናዊ የሆነ አገልግሎት ለደንበኞቹ መስጠት መጀመሩም ታውቋል ፡፡
የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም እ.ኢ.አ በ 1994 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ተቋሙም ወደ ስራ ከገባት ጊዜ አንስቶ በአነስተኛ የንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የብድርና የቁጠባ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ፡፡ የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአለማችን ብሎም በሀገራችን ኢትዮጲያ ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ በስራ እንቅስቃሴዎች ላይ መቀዛቀዝን ቢያስከትልም ተቋሙ የነበሩትን ችግሮች በመቋቋምና በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በጠበቀ መልኩ ከዚህ ቀደም ያከናውናቸው የነበሩትን የብድርና የቁጠባ አገልግሎት መስጠት ችሏል ፡፡
የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ 2013 ዓ.ም በተለይም በአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ 200 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ከ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ በላይ ደንበኞችን ለማፍራት አቅዶ በመስራት ላይ ሲሆን በመጀመሪያው ሩብ አመትም 41 ሚሊዮን ብር የሚሆን የብድር አገልግሎት መስጠት መቻሉን የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ አበበ ተናግረዋል ፡፡
ተቋሙ በያዝነው በጀት አመት 128 ሚሊዮን ብር ደንበኞቹ እንዲቆጥቡ ለማስደረግ ያቀደ ሲሆን በመጀመሪያው ሩብ አመትም ለማስቆጠብ የታቀደውን ያክል መቆጠብ መቻሉን ተናግረው ተቋሙ ከዚህ ቀደም ይሰራበትን የነበረውን አሰራር ዘመናዊ በሆነ አሰራር በመቀየር ለደንበኞቹ የሚሰጣቸውን አገልግሎት በሁሉም የተቋሙ ቅርንጫፎች የኮር ባንኪንግን በመጠቀም ፈጣንና ዘመናዊ የሆነ አገልግሎት እንደሚሰጥም አቶ ተሾመ ተናግረዋል ፡፡
የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለኢንዱስተሪው ዘርፍ ሰፊ መሰረትን የሚጥሉ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብሎም መለስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ ስራ ያልገቡ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ተቋሙ መስራት መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሱልጣን አሊዬ ተናግረዋል፡፡


