“ማህበራዊ እሴቶቻችንን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በአገራችን ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረው የአብሮነት ቀን ጥር 27 ቀን 2013 ዓ/ም በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚከበር የድሬዳዋ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ አስታወቁ፡፡
ኃላፊው እንደገለፁት የሚከበረው የአብሮነት ቀን ዋነኛ ዓላማ የድሬዳዋ ማህበረሰብ ያፈራውና የገነባውን ጠቃሚ ማህበራዊ ዕሴቶችን መልሶ መገንባት የሚያስችል ዝግጅት የሚከናወንበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም ድሬዳዋ የምትታወቅበትን የመቻቻል፣ የመፈቃቀር; የአንድነት; የመተሳሰብና የአብሮነት ዕሴቶቻችንን መልሰን ለመገንባት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በባለሙያዎች የተዘጋጁ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግ ሲሆን የአስተዳደሩ ከንቲባ፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ ወጣቶችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መሆኑን አቶ ሙራድ አስረድተዋል፡፡


