መግለጫውን ለሚዲያ የሰጡት የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ለውጥ ሥራዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ በእሳት አደጋው እሳቱን ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ሶስት የአከባቢው ሰዎች ላይ በጪስ የመታፈን ጉዳት የደረሰባቸውና በአሁን ወቅት በህክምና ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዉ ሌሎች ሁለት የእሳት አደጋ ፖሊስ አባላት ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱንም አስታውቀዋል፡፡
በእሳት አደጋው የጠፋው ንብረትም ፖሊስ አጣርቶ የጉዳቱን መጠን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ በእሳት አደጋው ከ2 ሚልየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት የወደመ ሲሆን በዝርዝር ኮማንደር ገመቹ ካቻ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡
በአምስት ግለሰቦች ላይ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆችና መጋዘኖች እንዲሁም መኖሪያ ቤት በእሳት አደጋው ወድመዋል
አቶ አብዲ መሀመድ የተባለ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ባለቤት አጠቃላይ ሱቁና መጋዘን ወደ 500 ሺህ ብር የሚገመት ንብረቱ ወድሟል፣ እንደዚሁም አቶ አብደላ መሀመድ ሱቅና መጋዘን ሙሉ በሙሉ ወድሞ ወደ 500 ብር ሺህ የሚገመት ንብረት ጠፍተዋል፣ አቶ ሸምሱ ከማል ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ሙሉ ለሙሉ የወደመ ሲሆን እንደዚሁም 500 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፣ ሌላው አቶ ናስር አብዲ መጋዘን ውስጡ የነበረው የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር እቃዎች ወደ 400 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፣ አቶ ታጁዲን ጀማል የተበለው ግለሰብ በመጋዘኑ ውስጥ የነበረው ሸቀጣ ሸቀጥ ዕቃዎች ግምታቸው ወደ 400 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ሌላው ተክሌ ትረሃስ የተባለ የባህል አልባሳት የሚሰራበትን መኖሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ የተቃጠለበት ሁኔታ ነው ያለው ግምቱ ያልታወቀ ንብረትም ወድሟል ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የእሳት አደጋ ዲቪዥን በፍጥነት ቦታው ደረሶ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል ለመቆጣጠር ተችሏል ብለዋል ከማንደር ገመቹ፡፡
ኮማንደር ገመቹ ካቻ አክሎም የእሳት አደጋው መንስኤ ፖሊስ እያጣራ መሆኑን ገልጾ ፖሊስ አጣርቶ የሚያሳውቅ ይሆናልም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የአስተዳደሩ ህብረተሰብ አከባቢያቸው በንቃት በመጠበቅ ከእንደዚህ ዓይነቱ የእሳት አደጋ በትላልቅ የገበያና የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች ላይ ተገቢው ጥበቃ እንዲያደረጉ አሳስቦ የተለየና አጠራጣሪ ነገር ቢያጋጥማቸው ለሚመለከተው የፖሊስ ኃይል የማሳወቅ ሥራ መሰራት ይገባል ብለዋል፡፡


