በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው::

    በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሁራን ሚና በሚል ርእስ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክሎኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
    መድረኩ ያዘጋጀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከአዳማ ሳይንስ እና ቴክሎኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው።
    በውይይቱ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ከአዳማ ሳይንስ እና ቴክሎኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ምሁራን እና ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ናቸው።
    በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ እምቅ የውሃ ሀብት፣ በውሃ ሀብት አጠቃቀም እና በሂደቱ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።
    በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ምክክር ይደረጋል ነው የተባለው።
    ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የምትከተላቸው ፖሊሲዎች እና አቅጣጫዎች ከዓለም አቀፍ ሕጎች፣ ደንቦች እና አሰራሮች ጋር ባላቸው ትስስር ዙሪያም ውይይት ይካሄዳል።
    በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ ትብብር ከውሃ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ያለው አስተዋጽኦም በመድረኩ ትኩረት ያገኛል ተብሏል።