ከይዞታቸው ለተነሱ 950 አባወራዎች በዛሬው እለት የመሬት ርክክብ ተካሄደ::

    በድሬደዋ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየው ለበርካታ አመታት ለመንግስት ለልማት ስራ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተነሱ ግለሰቦች በዛሬው እለት የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚገባቸውን የመሬት መጠን ለማስረከብ የእጣ ማንሳት ሰነ-ስርአት አካሄዷል፡፡
    በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ የአስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን እንደተናገሩት በዛሬው እለት የዕጣ ማንሳቱ ስነ-ስርአት የሚካሄደው ከዚህ ቀደም ለልማት ተነሺዎች የካሳና የመሬት ርክክብ ቢደረግም ተሰጠን ቦታ ተመጣጣኝ አይደለም በማለት ቀድሞ የነበሩበት ቦታ ተመልሰው በመስፈራቸው በጨረታ ያሸነፈው እንዳይሰራ በማድረጉ በጠየቁት ጥያቄ መሰረት ተመጣጣኝ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው በዛሬው እለት ርክክብ ተደርጓል ብለዋል፡፡
    96 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን በመጥቀስ ለ950 አባወራዎች የመኖሪያና የቢዝነስ ማእከላትን እንደሚይዝ ገልፀዋል፡፡
    በአካባቢው በአጭር ጊዜ ውስጥ የመሰረተ ልማት ለማሟላት የቅድመ ክፍያ የፈጸምንበት ሁኔታ አለ ያሉት ኃላፊው ቀሪዎችንም በቅደም ተከተል በማስኬድ የመሰረተ ልማቱን ለማሟላት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
    ርክክብ የፈጸሙት ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት ከረጅም ጊዜ በኋላ የነበረብን የመልካም አስተዳደር ችግር መፈታቱ እነዳስደሰታቸው በመግለጽ ቦታው ምንም አይነት የመሰረተ ልማት ስለሌለው በተገባላቸው ቃል መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል፡፡
    ከዚህም በተጨማሪ በተሰጣቸው መሬት አካባቢ የጎርፍ መሄጃ በመኖሩ ለሱም አስተዳደሩ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡