በተከሳሽና በምሰክር አለመቅረብ ምክንያት የሚቋረጡ መዛግብት መነሻ በማድረግ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ እና የመፍትሄ እርምጃዎችን በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ የጋራ ምክክር መድረክ ተካሄደ
በዳሰሳ ጥናቱ ላይ በዋንኛነት የቀረበው በአስተዳደራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከመርማሪ ፖሊስ እስከ ፍርድ አሰጣጡ ድረስ ያሉት ተግዳሮቶች የፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ድርሻ እንደሆነ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመልክተዋል፡፡
በጥናቱ መሰረትም የተከሳሽ መጥፋት፣ የምስክሮች ማመላለስ እንዲሁም የአስገዳጅ የመርማሪ ቡድኑ የግባዓት አለመሟላት ችግሮች የተፈለገውን የፍትህ ስርዓት ለማረጋገጥ እንደማያስችል ተነስተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት የአስተዳደሩ የከተማና የገጠር ፖሊስ ጣቢያ መርማሪዎችና አቃቤ ህግ የተከሳሾች የዋስ አሰጣጥ፣ የምስክሮች እንግልት፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የችሎት ዳኞችን ያለ መምጣት የፍርድ ሂደቱን አሰልቺ እንዲሆን ከማደረጉም በላይ ተገቢውን ፍትህ እንዳይሰጥ ምክንያት ሆነዋል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፈይሳ ሹርኬ የህግ ማስከበር ስርዓቱ ላይ የፖሊስ የአቃቤ ህግና የፍርድ ቤት ሚና ተለይቶ የተቀመጠ ቢሆንም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቋረጡ የክስ መዛግብቶች በምስክርና በተከሳሽ ባለመቅረብ እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ ይህንም ችግሮቹን በጥናት ተለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀመጥላቸው በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ቀርቧል ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ የፍትህና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ ጣሃ በበኩላቸው በአስተዳደሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት የአስተዳደራችን የፍትህ ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደነበረና በቀጣይ ተቋማቱ በሰው ሃይልና በግብዓት ተሟልቶ ተገቢውን የፍትህ ስርዓት በአስተዳደሩ እንዲረጋገጥ በተለይም የዚህ ጥናት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተነሱት ምክረ ሀሳቦች በቀጣይ የጥናቱ የመፍትሄ አቅጣጫ ሆነው ይቀርባሉ ተብለዋል፡፡


